59.29 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺአርፎ ያልተኛበት ተስፋና ድካሙ ፣ ሊፈታ ነው መሰል የቴዎድሮስ ህልሙ”

ʺአርፎ ያልተኛበት ተስፋና ድካሙ

ሊፈታ ነው መሰል የቴዎድሮስ ህልሙ”

ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) እመቤቷ ተዋበች መልካም ልጅ ወለደች፣ በፍቅር አሳደገች፣ በጥበብ አነፀች፣ ራዕይ አሰነቀች፣ ጥበባትን እንዲመረምር መብራት ሆነች፡፡ ኃያሉ ሠው በቋራ ተነሳ፡፡ ራዕዩ ሩቅ፣ አንደበቱ መረቅ፣ ንግግሩ ልብ የሚሰርቅ፣ በጥበብ የሚራቀቅ፣ ለሀገር ክብርና አንድነት የሚዋደቅ፤ ሀገሩን የሚወድ፣ በሚዛን የሚፈርድ፤ የተበደለን ሀገር እንዲክስ፣ የረቀቀን ጥበብ በብልሃት እንዲምስ፣ ከጥበብ እንዲያቀምስ፣ ለአንድነት እንዲነግሥ ካሳ አሉት፡፡ ሀገሩን ካሰ፣ በግርማ ነገሠ፣ ወደ ጥበብ ገሰገሰ፣ ፅናት ፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አርቆ አሳቢነትና በሀገር መኩራት አወረሰ፡፡

በየአድባራቱና በየገዳማቱ እየተዘዋወረ የቀሰማቸው ጥበቦች ከዘመኑ አስቀደሙት፤ ዕውን የዚህ ዘመን ሰው ነውን አስባሉት፡፡ ʺ በተሳሳተው ጊዜ የተገኘው ትክክለኛው ሰው” ሲሉም ጠሩት፡፡ የዘመነ መሳፍንት በትር የጎዳት ሀገሩ አሳዘነችው፣ ካሳ ሆይ ተነስና አንድነትን መልስ ስትል ሀገሩ ጠራችው፡፡ ገና በማለዳው የሀገሩን ጥሪ ሰማ፣ አንድ ሊያደርጋት ከራሱ ጋር ተስማማ፡፡ በቀን ይሁን በጨለማ ለኢትዮጵያ እማማ ተግቶ ሊሠራ ወደደ፡፡

የቀሰመው ትምህርት የላቀ ዕውቀት፣ ብልሃት፣ መልካም ሥርዓት አስተማረው፡፡ የቋራን በረሃ ቤቱ፣ ስለኢትዮጵያ ሳያቋርጥ ማሰብ ሕይወቱ ሆነ፡፡ ዝናው ገነነ፡፡ አስቀድሞ የተመረጠ ነውና ግርማው አስፈሪ ሆነ፡፡ መሳፍንቱ ልባቸውን ተጠራጠሩት፣ ካሳን በስጋት ተመለከቱት፣ ግዛቷን እያሰፋች የዓባይን ምንጭ ለመያዝ የምታልመው ግብጽ ዝናውን ሰማች፡፡ ተስፋዋን በአጭር የሚቀጭ ኃያል ነውና ፈራች፡፡ ራደች፡፡ ታናሽ ታላቁ፣ ሊቁም ደቂቁም ʺካሳ ካሳ” ይል ጀመር፡፡ ይነግሥ ዘንድ ተመኙለት፣ የራዩን ሥራ ጀመረ፡፡ የአባቱን ሀገር ቋራን ተቆጣጠረ፡፡ የመሳፍንቱ ስጋት ጨመረ፡፡

ኃያሉን ካሳ የሚያቆመው ጠፋ፡፡ ግዛቱን እያሰፋ ክብሩና ዝናው እየጨመረ ሄደ፡፡ እቴጌ መነን ተደናገጡ፡፡ እቴጌዋ ብልህ ሴት ናቸው፡፡ የካሳ ጀግንነት አስቀድሞ ግብቷቸዋል፡፡ በቋራ የሚመጣውን የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላት እየቀጣ ስሙ ናኝቷልና፡፡ መነን ‹‹ ምከሩ እንጂ ይሄን ቆለኛ ምን ብናደርገው ይሻላል?›› ይሉ ጀመር፡፡ ምክሩ ካሳን መውጋት ነበር፡፡ ደጅ አዝማች ወንድይራድ ካሳን እንዲወጋ ተላከ፡፡ ካሳን ካሸነፈ ልዕልቷን ተዋበችን እንደሚያገባ ቃል ተሰጠው፡፡ የተባለው ሁሉ አልሆነም ድል ለካሳ ሆነች፡፡ ካሳን ለመዛመድ ተዋበችን ዳሩለት፡፡ ተዋበች የራዕዩ ደጋፊ፣ ስለ ክብር ከፊት ተሰላፊ ሆነች፡፡

ባለ ራዕዩ መሪ ጀግንነቱን በብልሃት ይመራው ጀመር፡፡ የካሳና የእነ እቴጌ መነን የፍቅር ጊዜ ረጅም አልሆነም፡፡ ጥል ተፈጠረ፡፡ ተዋበች ግን ከፍቅሯና ከክብሯ ጋር ነበረች፡፡ ካሳ ሳይነግሥ እንደማይመለስ ሀገሬው አወቀ፡፡ ተወደደ፡፡ የሀገሬው ሰው ለእርሱ ይቀበለው ጀመር፡፡ ከቋራ አልፎ ድንቢያንም ያዘ፡፡ የሚገጥሙት ስመ ጥር መሳፍንት ሁሉ ከፊቱ አልቆም አሉ፡፡ በግርማው አራዳቸው፣ በክንዱ ጣላቸው፡፡ ካሳ ድል በድል እየሆነ ከነገሥታቱ ከተማ ጎንደር ከቤተ መንግሥቱ ገባ፡፡ ታማኝ የጦር መሪዎቹ አብረውት ነበሩ፡፡

ጎንደር ሲገባ ሕዝቡ እልል እያለ ተቀበለው፡፡ ሕዝቡም ‹‹ ስምህን ንገረን ስምህን?›› ሲለው ‹‹ስሜን ሰሜን እነግራችኋለሁ›› አላቸው ይባላል፡፡ ዘመቻዎቹ ሁሉ በድል የታጀቡ ሆኑ፡፡ ወደ ሰሜንም ሄደ፡፡ ድል ቀናው፡፡ በደረስጌ ማርያም ታላቁን ዘውድ ደፋ፡፡ የአንድነቱ መሪ ነገሰባት፤ ካሳ ንጉሠ ነገሥት ዚትዮጵያ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ ነገሠ፡፡

ቴዎድሮስ መመኪያው ፈጣሪው ነው፡፡ ‹‹ ከትቢያ አንስቶ ለክብር ያበቃኝ እግዚአብሔር ይከበር ይመስገን›› እያለ ዘወትር ፈጣሪውን ያመሰግናል ይሉታል፡፡ በጌታው እየተመካ ሀገሩ ኢትዮጵያን የዘመነች፣ የጠነከረች እንድትሆን ይጥር ጀመር፤ በዚህ ብቻ አላቆመም ኢየሩሳሌምንም ነፃ ለማጣት ራዕይ ሰነቀ፡፡

ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር እነሆ ጀግና በሚለው መጽሐፋቸው ” እኔን የሚያስደንቀኝና ‹ምነው ስለሱ ብዙ ብዙ ባወቅኩ!› የሚያሰኘኝ የሰውየው የካሳ ባሕሪ ነው፡፡ እኔን በዘመናት ርቀት ይህን ያህል ያስደነቀኝ ይኼ ካሳ የሚሉት ሰውዬ አብረውት የኖሩትን ምን ያህል አስደነቃቸው? እስከ መጨረሻው እስኪሞቱለት ድረስ፡፡ ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንመለከት ነው ሰውዬው የሚታየን›› ብለዋል፡፡ እርሱ አስደናቂ ነው፡፡ በአስደናቂነቱም ቀጠለ፡፡

ኃያሉ ቴዎድሮስ ከውጭ አገር የመጣ ሰው ሲያገኝ ቀዳሚው ጥያቄው “ምን ሥራ ታውቃለህ ?” ማለት ነበር ይሉታል። ጥበበኛ ሰው ሲያገኝም ሳይንቅ ይማራል፤ ለሚወዳቸው የሀገሩ ሕዝቦች ሊያስተምር ይጥራል፡፡ ቴዎድሮስ አንድ ጠንካራና ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደርን መመስረት ይሻል፡፡ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቃና በውጊያ ጥበብ የተካነ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊትም ይፈልጋል፡፡ ጥበበኛ መሪ፣ ጥበበኛ ወታደር፣ የማትደፈር ሀገር መመሥረት ህልሙ ነበርና ህልሙን ዕውን ያደርግ ዘንድ ጥረቱን ቀጠለ፡፡

በኢትዮጵያ ዳር ድንበር እያንዣበበ የሀገሩን ክብር ሊደፈር የሚሻን ጠላት መክቶ፣ የተፈራችና የተከበረች ሀገር ለመገንባት መዘመን ወሳኙ ጉዳይ እንደሆነ አስቀድሞ ታውቆታል፡፡ የውጭና የውስጥ ጠላቶቹ ግን እንዳሻው አልስሄድ አሉት፡፡ ያም ሆኖ ራዕዩን ይኖር ዘንድ ሳይሰለች ታተረ፡፡

ከነብሱ አስበልጦ የሚወዳት ኢትዮጵያ የዘመነ ጦር ይኖራት ዘንድ ከአውሮፓ በተለይም ከእግሊዝ መንግሥት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት አደረገ፡፡ ባሰበው ልክ ባይሆንለትም ራዕዩን ፈተነ፡፡ ከጥንታዊቷ ከተማ ደብረታቦር በስተ ሰሜን ምሥራቅ በኩል ለመቅደም የታደለች፣ ለመዘመን የተፈጠረች የምትመስለዋ ቀዳሚው ኢንዱስትሪ አሀዱ ተባለባት፡፡ ይሄም የአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ ናት ይሏታል- ጋፋት፡፡ የዚያ ጊዜ ዘመናዊት ጋፋት ቴዎድሮስ ላሰበው ዘመናዊ መሳሪያ መሥሪያ የሚሆን አፈር ያለው መሆን፣ የአካባቢው ወሳኝ ሥፍራ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች አስመረጣት ይላሉ፡፡

ሥራው እንዲጀመር ታዘዘ። በትዕዛዙም መሠረት ወደ ሥራ ተገባ ። ቴዎድሮስ የሚመኘው ዘመናዊ መሳሪያ እውን ሊሆን ይመስላል፡፡ የብረት ማቅለጫውን ምድጃ ከሸክላ እንዲሠራ ተወሰነ። በየ ሀገሩ እየተዞረ ለሸክላ መሥሪያ የሚሆን አፈር ይፈልጉ ጀመር። የታሰበው እየሆነ ሄደ፡፡ ደስታ ሆነ። ንጉሡም እየተመላለሰ በማየት ውጤቱን ይጠብቅ ነበር፡፡ ጥበበኞቹን ያጠናክራል፤ ብርቱ ነውና ብርታት ይሰጣቸዋል፡፡ ራዕዩን በዓይኑ እያዬ ሲሄድ ጥበበኞቹን “ልጆቸ” እያለ ይጠራቸው ጀመር ይባላል።

በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ድንቅ ነገር ተሠራ፡፡ ደስታ ሆነ፡፡ ንጉሥም ተደሠተ፡፡ የንጉሡ ራዕይ በእውን ታየ፡፡ መድፉ ተሠራ፡፡ ቴዎድሮስ በተሠራው ዘመናዊ መሳሪያ ሀገሩን ሳያስደፍር፣ በአንድነት ሲኖር ታዬውና ደስታው እጥፍ ሆነ፡፡ “ዘላለም መመኪያዬ እግዚአብሔር ነው” የሚለው ቴዎድሮስ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ ጥበበኞቹንም አመሰገናቸው፡፡ በመድፍ ሥራው ላይ ለተካፈሉት የክብር ቀሚስ፣ በወርቅና በብር ያጌጠ ፈረስና በቅሎ ሸለማቸው። ብርም ተሠጡ። ቴዎድሮስ መድፉ ተተኩሶ ምን ያህል ርቀት መምታት እንደሚችል ለማየት ፈለገ። ተኩሱ በሚሞከርበት ቀንም ወደ ጋፋት ሄደ። ኃያሉ ሰው ሕልማቸው በእውን አይተዋል፣ ተተኩሶ በፈለጉበት ዓላማ እስኪያውሉት ድረስ ጓጉተዋል፡፡ ተተኮሰ፡፡ ሠራም፡፡ ሌላ ደስታ ሆነ፡፡

ቴዎድሮስ ለሀገሩ ሳይሰለች ይደከም ጀመር፡፡ ፈተናዎቹና መከራዎቹ ግን ጸኑበት፡፡ ልቡ ውስጥ ያበጃጃትን ኢትዮጵያ በእውን ያያት ዘንድ የሚቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ ራዕዩን ይኖር ዘንድ ረጅም እድሜ አልታደለውም፡፡ ለቴዎድሮስ እጅ መስጠት ነውር፣ ስለ ሀገር ኖሮ ስለ ሀገር መሞት ክብር ነበርና ከፍ ካለው ተራራ ከፍ ያለው ሰው ራሱን ሰዋ፡፡

ʺአትንኩኝ ባይል እንጂ ባሩዱን ተጠምቶ

መቅደላ ላይ ጠጣው ጎንደር አስቀድቶ” እንዳለች ከያኟ ራዕዩን እንደያዘ፣ በብዙው እንዳለመው፣ በትንሹ እንደጀመረው፣ በሰፊው ሳይኖረው፣ በባሩድ ሸፈነው፡፡ ከዘመናት በኋላ የቴዎድሮስ ጅማሮ ሊቀጥል ይመስላል፡፡

ʺአርፎ ያልተኛበት ተስፋና ድካሙ

ሊፈታ ነው መሰል የቴዎድሮስ ህልሙ” መልካም ራዕይ አይጠፋምና የቴዎድሮስ ዘመናዊት ሀገር መፍጠር ራዕይ ማብሰሪያ፣ የአፍሪካ ኢንዱስትሪ መጀመሪያ፣ የጥበብ መቀመሪያ የነበረችው ጋፋት አልተዘነጋችም፡፡

እንደ ጋፋት ራዕይ ይዞ ለዘመናት ተደብቆ የኖረ የሚገኝ አይመስልም፡፡ ጋፋት ኃያሉን ንጉሥ አብዝታ ጠበቀች፣ አልተመለሰም፡፡ ስሙ ግን አፈር አለበሰም፣ ልጆቹን ጠበቀች ዘገዩባት፣ ተስፋ ሳትቆርጥ ጠበቀቻቸው፣ ዘመን ዘመን እየተካ ሲሄድ አብዝታ ናፈቀቻቸው፡፡ ያይዋት ዘንድ ሄዱላት፡፡

ጋፋትን ከተደበቀበት ለማውጣት በጎንደርና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን ባሕል ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ገዳፈው ወርቁ ነግረውኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ጥረት መልካም ቢሆንም ዘመናዊቷን ጋፋት ግን መመለስ ሳይቻል ዓመታት አልፈዋል፡፡

በቅርቡ የተደረገው ስምምነት የቴዎድሮስን ራዕይ ከተደበቀበት ሊያወጣ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ያን ጊዜ ቴዎድሮስ ያሰመራቸው መስመሮች መጓዣ ይሆናሉ፡፡ የቴዎድሮስ የጥበብ ቁልፎች ዘመንን ይከፍታሉ፡፡ ለዚያው ያብቃን፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በክልሉ 13 ዞኖች የወባ በሽታ በስፋት እንደሚገኝ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አስታወቀ

admin

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 10ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል” የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት

admin

እስከ ታችኛው መዋቅር ያለውን አሰራር በመቀየር ገፊ የኢንቨስትመንት አሰራር ማነቆዎችን ማሻሻል ይገባል – የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

admin