78.37 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺአልጎድል ስላለ ብለውት ብለውት የመከራውን ጎርፍ በደም ተሻገሩት”
ʺአልጎድል ስላለ ብለውት ብለውት
የመከራውን ጎርፍ በደም ተሻገሩት”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቅ ምድር፣ የስልጣኔ በር፣ የነጻነት ዋልታና ማገር፣ የእንቁዎች ሀገር፣
ያልተፈታች፣ ያልተደረሰባት፣ የማይደረስባት ድብቅ ሚስጥር፤ ምድራዊያን ለክፋት ሰማያዊያን ለበረከትና ለድኅነት ይመለከቷታል፡፡
ወጀብ ሲቀርብ መጋረጃ፣ መንገድ ሲዘጋ መራመጃ፣ ሲቆሽሽ ማጽጃ አጥታ አታውቅም፡፡ ከቀደሙት ሁሉ ቀድማ የራቀች፣ ኃያላን ነን
ከሚሉት በላይ ኃያል የሆነች፣ በመከራውም በመልካሙም ዘመን የፀናች፣ ከአለት የጠነከረች፤ በፈተናዎች ሁሉ ያልተሸነፈች ናት፡፡
ኃያላን ነን ባይ መንግሥታት ከመፈጠራቸው አስቀድሞ የመንግሥትነት ታሪክ ያካበተች፡፡ ስልጡን ነን ባዮች ሀገር ከመሆናቸው
አስቀድማ አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀች፣ መቅደስ የቀረፀች፣ መስጂድ ያነጸች፣ የራሷን ፊደል ያዘጋጀች፣ በሉዓላዊነቷ የተከበረች፣
የዓለም ስልጣኔ በር የሆነች፣ አብያተ መንግሥታትን በጥበብ የሠራች፤ በእልፍ የመከራ ጊዜ መካከል በድል የተሻገረች ሀገር ናት
ኢትዮጵያ፡፡ የኢትዮጵያ ኃያልነትና አይነኬነት የማይገባቸው፣ ጽናቷ የማይስማማቸው ሁሉ በየዘመናቱ ኃይላቸውን እያደራጁ ሳንጃ
ስበው፣ ጦር መዘው ሊወጓት ከጅለዋል፡፡ ታዲያ ሁሉም ተሸነፈዋል፤ አንዳቸውም የኢትዮጵያን ነጻነት መንጠቅ አልተቻላቸውም፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውንና ክብራቸውን በተነኩ ቁጥር በባዶ እግራቸው እየገሰገሱ፣ እንደ አንበሳ እያገሱ፣ አጥንታቸውን
እየከሰከሱ፣ ደማቸውን እያፈሰሱ ጠላታቸውን አሳፍረዋል፡፡ ኢትዮጵያን የነካ ሁሉ እጣ ፋንታው በዱር በገደሉ በሳንጃ እየተባለ፣
በጥይት እየተቆላ፣ የአራዊት ቀለብ ሆኖ መቅረት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነጻነት፣ ኢትዮጵያዊነት ብርታት፣ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት፣
ኢትዮጵያዊነት አርቆ አሳቢነት፣ ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ ኢትዮጵያዊነት ታማኝት፣ ኢትዮጵያዊነት
ዘላቂነት፣ ኢትዮጵያዊነት ሰበዓዊነት ነውና ኢትዮጵያን የሚጠላት እንጂ የሚጥላት አይገኝም፡፡
ኢትዮጵያ የማትወድቅ፣ በወርቅ ቀለም የተጻፈው ታሪኳ የማይለቅ፣ የጀግንነት ታሪኳ እየቆዬ የሚደምቅ እንጂ ጠላቶቿ እንደሚሉት
በወጀብ የሚፈርስ፣ በድንገት የሚገረሰስ፣ ፊት የቀደመው ታሪኳ ወደኋላ የሚመለስ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የነኩ ሁሉ ታሪካቸውን
እያጠፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ከፍ አድርገው እየጻፉ ይመለሳሉ፡፡ የውስጥም ኾነ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ ነካክተዋል፡፡
ዳሩ ሁሉም ተንኮታኩተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ነካክታ በአውሮፓ የገነነውን ስሟን አጥፍታ የተመለሰችው ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ
ከተነሱት የውጭ ጠላቶች ተርታ ከቀዳሚዎቹ ትሰለፋለች፡፡
በቀኝ ግዛት አባዜ የተለከፉት የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን እያስነሱ ወደ አውሮፓና ኢሲያ አህጉራት ይዘምቱ ነበር፡፡ ብዙ ሀገራት
ቀድመው ተሸንፈው ይጠብቁ ነበርና ቀኝ ገዢዎቹ ኪሰራ ሳይገጥማቸው ግዛታቸውን ያሰፋሉ፤ ኃያልነታቸውንም ከፍ ያደርጋሉ፡፡
ነጻነታቸውን አናስነካም ብለው የተዋደቁትም የኃይል ሚዛናቸው አናሳ ስለሚሆን የማይቀረውን ግዛት አምነው ይቀበሉ ነበር፡፡
መነሻውን አውሮፓ አድርጎ በዓለም ሀገራት የተጥለቀለቀው የቀኝ ግዛት ማዕበል አፍሪካን አላበሳት፡፡ ነገር ግን አፍሪካ ሙሉ
ለሙሉ በማዕበሉ አልጠፋችም ነበር፡፡ በአፍሪካ ምሥራቅ ንፍቅ በቀንዱ በኩል ሊወጋት የመጣውን ሁሉ የምትመከት አንዲት
ሀገር ነበረች፡፡
ይህች ሀገር የቀኝ ግዛት ጨለማ ዙሪያ ገባዋን ከቧታል፡፡ የአፍሪካውያን ጸሐይ ጨርሳ ልትጠልቅ በእርሷ ሰማይ ላይ ብቻ
ቀርታለች፡፡ ከአውሮፓ የተነሳው ማዕበልም እርሷን አዳፍኖ የቀኝ ግዛት ውቅያኖስ ሊሆን እርሷን ብቻ መያዝ ቀርቶታል፡፡
ʺ የጥቁሮቹን ሀገር አፍሪካን በረደው
ኢትዮጵያዊ አይደል አልፎ ሚጋረደው” እየተባለ በነጻነት ማጣት የበረዳትን አፍሪካን የማዳን፣ የራስን ሀገር ሉዓላዊነት ያለ
ማስደፈር ተጋድሎ ከኢትዮጵያዊያን ላይ ደረሰ፡፡ ማዕበሉ ገፋ፤ የኢትዮጵያን ድንበር አለፈ፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን በአንድ አዋጅ
ተሰባስበው ማዕበሉ አልፎ ወደፈሰሰበት ስፍራ ተመሙ፡፡ በአባዳኘው የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን
ለጦር ሰጥቶ በወኔ ገሰገሰ፡፡ የጀግንነት መለኪያ ቀን ደረሰ፡፡ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ምድር ታመሰች፡፡ አቧራ ለበሰች፡፡ በደም ራሰች፡፡
በደንብ የተሳለው የኢትዮጵያውያን ጎራዴ የጠላትን አንገት ይቀነጥሰው ጀመር፡፡ አፍሪካን አጥለቅልቆ፣ የአፍሪካውያን ጀንበር
አጥልቆ ሊፈፅም ጥቂት የቀረው የአውሮፓ የቀኝ ግዛት አባዜ አደጋ ገጠመው፡፡ የጣልያን ወራሪ ኃይል ተደመሰሰ፡፡
ኢትዮጵያውያን ማዕበሉን በድንበር መለሱት፣ በአፍሪካ ምድር ላይ የነበረውን ጨለማ ገፈፉት፣ የማይጠፋውን ብርሃን በዓድዋ
ተራራ ላይ አበሩት፣ የአውሮፓውያንን የቀኝ ግዛት ምንጭ አደረቁት፡፡ ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን ስታስከብር፣ የአፍሪካ ነጻነትን ቀን
ስታበስር ኃያላኑ ደነገጡ፡፡ ኢትዮጵያ ባሰመረችው መስመር፣ ኢትዮጵያ በለኮሰችው ብርሃን ተሻግሮ የሚሄደው ብዝቶባቸዋልና፡፡
ኃያልነታቸውን በአንድ ጀንበር ያጡት፤ ለዘመናት የገነቡትን ዝና የገረሰሱት ጣልያኖች እያለቀሱ ብቻ አልተቀመጡም፡፡ ሌላ እድል
ሊሞክሩ መጡ እንጂ፡፡ አርባ ዓመታትን ጠብቀው ተዋርደው ወደተመለሱባት ሀገር ዘለቁ፡፡ ሌላ ጦርነት ሌላ ጀብዱ ተጀመረ፡፡
ጣልያን ከወትሮው የኃይል አሰላለፍ የተለዬች ሆና መጣች፡፡ እንደ ዓድዋው ሁሉ በአንድ ጀንበር የሚጠናቀቅ አልነበረም፡፡
የጦርነቱ ጊዜ እየጨመረ ሄደ፡፡ ድንበር ተሻግሮ ከመጣው የኢትዮጵያ ጣላት ያልተናነሰ፤ የውስጥ ከሃዲ የኢትዮጵያን አርበኞች
ይወጋቸው ነበር፡፡ ቀን ቀንን እየተካ ወራት ተከታትለው ዓመታት ዘለቁ፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው ጥይት
ከመተኮስ፣ በጎራዴ አንገት ከመቀንጠስ ያቆሙበት ቀን አልነበረም፡፡ ተጋድሎው ቀጠለ፡፡
በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ የጦር አማካሪና ተዋጊ በነበረው አዶልፍ ፓርልሳክ የተጻፈውና የአበሻ ጀብዱ ተብሎ በተጫነ
ጆብሬ በተተረጎመው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በባዶ እግራቸው ዘመን ባለፈበት መሳሪያ ዘመናዊ መሳሪያ የያዘውን ጦር
ያርበደብዱት እንደነበር ጽፏል፡፡ መትረጌስ የሚተኩሰውን የጠላት ጦር ያለ ምንም ፍርሐት ጎራዴያቸውን ስለው በመገስገስ
አምስት ሲወድቅ፣ አስር እየተተካ፣ አስር ሲወድቅ ሃያ እያለፈ ዘመናዊ ጦር የታጠቀውን ጠላት አንገቱን በጎራዴ ይቀነጥሱት
እንደነበር ከትቧል፡፡ ጀግንነታቸው ወደር የለሽ መሆኑን በመጽሐፉ ላይ አስፍሯል፡፡ የውስጥ ባንዳዎች ባይኖሩበት ኖሮ ጦርነቱ
ረጅም ጊዜ እንደማይወስድም ተናግሯል፡፡
ሌላኛው በጣልያን ወረራ ጊዜ ከኢትጵያውያን ጎን በመሰለፍ የተዋጋው ኮሎኔል አሌኸንድሮ ዴል ባዬ ʺጎራዴ ይዞ የሚገሰግሰውን
የኢትዮጵያን ሠራዊት ማስቆም የሞላን ጎርፍ እንደመገድብ ይቆጠራል፡፡ አይቻልም” ብሏል፡፡ ይሄው ወታደርና ጸሐፊ ኢትዮጵያውያን
የጣልያን ወታደር ከአውሮፕላን የሚጥላቸውን ቦንቦች በጎራዴ ይቀበሏቸው እንደነበር ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ በደም የጸናች፣
በኅብረት የተከበረች፣ በአሸናፊነት የታጀበች ናት፤ ለዚህም ጀግኖቿ የፈፀሙት ጀብዱ ምስክር ነው፡፡ ለዚህም ነው ጦርነት
እንዳይመጣ ታግሰው ታግሰው አልሆን ሲላቸው መከራውን በደም ይሻገሩታል፡፡ ለዚህም ነው
ʺአልጎድል ስላለ ብለውት ብለውት
የመከራውን ጎርፍ በደም ተሻገሩት” የተባለላቸው፡፡
በአምስት አመቱ የጣልያን ወረራ ጀግኖች አርበኞች እንቅልፍ አልነበራቸውም፡፡ የጣልያን ወራሪ በሀገሪቱ ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ
ያደርጉት ነበር፡፡ እልፍ የሆኑ አርበኞች በየቦታው ለነጻነታቸው ተጋድለው በሚያዚያ 27 የወረደውን ሠንደቅ በሚያዚያ 27 ከፍ
አድርገው ሰቀሉት፡፡ የጣልያንን ሠራዊትም በዱር በገደሉ አስቀሩት፤ የተረፈውንም ከሀገራቸው ጠራርገው አስወጡት፡፡ በሪሁን
ከበደ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በሚለው መጻሕፋቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ጥር 12/1933 ዓ.ም ከሡዳን ጠረፍ ሮዛይረስ ከተባለው
ከተማ ተነስተው ጠላትን እየመቱ ሚያዚያ 27/1933 ዓ.ም በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ገቡ ብለዋል፡፡ ʺለአፄ ኃይለ ሥላሴ
በ1923 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘውድ ከጫኑበት ይልቅ ከአምስት ዓመት በኋላ በዙፋናቸው የተቀመጡበት ቀን
ለእርሳቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠች ደስታ ለመሆኗ የሚያጠራጥር የለም” ሲሉ አስፍረዋል በሪሁን ከበደ፡፡
በሁለቱ የጣልያን ጦርነቶች ጀግኖች አርበኞችን ያሳረፈ አንድ ድንኳን አለ፡፡ ስሙም ደስታ ይባላል፡፡ ጃንሆይ ከካርቱም ተነስተው
ሮዛይረስ ገብተው አዲስ አበባ እስኪደርሱ ድረስ አርበኞችን ይቀበሉ የነበረው በዚህ ድንኳን ነው፡፡ ደስታ የተባለው ድንኳን የአፄ
ምኒልክ ነው፡፡ ድንኳኑ አፄ ምኒልክ ጣልያንን ዓድዋ ላይ ድል ካደረጉ በኋላ ግዳይ፣ ምርኮኛ የተቀበሉበት ነው፡፡ ከአርበኞቻቸው
የድል ፉከራና ሽለላም ሰምተውበታል፡፡ ድላቸውንም አክብረውበታል፡፡ ጣልያን በዚያ ድንኳን ላይ ቂም ቋጥራለች የእርሷ ሀዘን
የኢትዮጵያ ደስታ ተክብሮበታልና፡፡ በ1928 ዓ.ም ተመልሳ ስትመጣና ግርማዋ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሀገር ሲወጡ ታሪካዊውን
ድንኳን ይዘውት ወጡ፡፡ ሲመለሱም ይዘውት ተመለሱ፡፡ ድንኳኑም ሌላ ደስታ ተከበረበት፡፡ ʺ ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” የሚል
ጽሑፍም ነበረበት፡፡ ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ ድል አድርጋ በደስታ ታከብራለች፡፡
ʺጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር፣
ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እንዲከበር ፣
እንሸከማለን የመከራ ቀንበር” እንዳሉ አርበኞች በዚያ ዘመን የነበረውን የመከራ ቀንበር ተሸክመው አልፈዋል፡፡ አሁንስ ? መልካም
የድል በዓል ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ፎቶ፡ ከድረ ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous articleደጅአዝማች ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ማን ናቸው?
Next article“ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያዊ ሌተናል ጀነራል”


Source link

Related posts

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 550 ከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮችን አስመረቀ

admin

የብሔር ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

admin

ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና በአንድነት ልንመክት ይገባል -አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

admin