76.68 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺበጽናት አብር በብልሃት ተሻገር” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

ʺበጽናት አብር በብልሃት ተሻገር”

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሁሉም ቀደመች፣ ብርሃን አሳዬች፣ ጨለማውን ገፈፈች፣ ተስፋን እውን አደረገች፡፡ ለምስክር፣ ለክብር፣ ለፍቅር የተዘጋጄች፡፡ አልፋ አትነካም፣ አሻግራ አታስነካም፡፡ መልካሟ ሀገር ቆራጥ ወታደር፣ ድንበር የሚያስከብር አጥታ አታውቅም፡፡ የጀግንነታቸውን ዝና ዓለም ያውቀዋል፣ አውቆም ያደንቀዋል፤ ገሚሱ በዝናቸው ሲሸበር፣ ገሚሱ ደግሞ በፍቅር ይወድቃል፡፡ ሀገረ ቀደምት፣ ፍፁም ጽናት፣ ግሩም አንድነት ያለባት፣ ቅዱስ መንፈስ ያረፈባት፣ ሰውና ፈጣሪ በአንድት የሚጠብቋት ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያ፡፡

በጥልቀት ያወቋት ይወዷታል፣ በቅናት የተመለከቷት ይጠሏታል፣ ጥበብን የሚሹ፣ ዓለምን የሚያስሱ ሁሉ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያዞራሉ፤ አንደበታቸው ስለ ኢትዮጵያ መልካምነት ይናገራል፣ ጀሯቸው ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገርን ይሰማ ዘንድ ይመኛል፤ ዓይናቸው ኢትዮጵያን ያይ ዘንድ ይቸኩላል፤ መልካም ነገር በእርሷ አለና፡፡ ኢትዮጵያ ቀደመች እንጂ አልተቀደመችም፣ አሸነፈች እንጂ አልተሸነፈችም፣ የዓለምን መንገድ ቀየሰች እንጂ በተቀየሰላት መንገድ አልተራመደችም፤ በማይመስላት መንገድ ተጓዥ ያላትን ሁሉ አልተቀበለችም፡፡

እርሷን አይቶ የፀና፣ እርሷን አይቶ የቀና ብዙ ነው፡፡ በእርሷ መንገድ ጥቁር ሁሉ ተሻግሯል፤ በእርሷ ክንድ የጠላት ገደል ተንዷል፣ ተሰባብሯል፤ ተገርስሷል፣ በእርሷ ጀብዱ የቅኝ ገዥ ዕቅድ ከሽፏል፤ የእርሷ ድል የዓለምን መንገድ አስተካክሏል፤ ኢትዮጵያ ከቀደሙት የቀደመች፣ ለድል የተፈጠረች፣ ሚስጥራዊት ሀገር ናት፡፡ ብዙ የመከራ ማዕበሎችን በጽናት ተሻግራለች፣ ብዙ የችግር ዘመናትን በአንድነት አልፋለች፣ ከባባድ ፈተናዎችን ተፈትናለች፣ ሁሉንም በጥበብ አልፋቸዋለች፣ ኢትዮጵያዊያን ወዳጃቸውን በፍቅር ባሕር ውስጥ ያሰምጣሉ፣ ጣላታቸውን በጦር በጋሻ ይጥላሉ፡፡ በፍቅር የመጣ ከበረከታቸው ማዕድ ይበላል፣ በጥል የመጣ ደግሞ በጥይታቸው ምጣድ ይቆላል፡፡ አመላለሱ ሁሉ እንደ አመጣጡ ነው፡፡

ዘመናትን በጽናትና በአንድነት የመጣችው ኢትዮጵያ ዛሬም ሌላ ዘመን መጥቶ ፈተናዎች አጋጥመዋታል፡፡ መፈተኗ አዲስ አይደለም፤ ማለፏም እንደዚያው፡፡ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ በሀገር ፍቅር መፅናት፣ ትዕግስት፣ አርቆ አሳቢነትና ራስን ከሀገር በፊት መስጠት ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን ያለፈችባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ʺትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ” እንዳለ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር ታሪክ ሰርተዋል፣ እርስ በእርሳቸው እየተዋደዱ በኅብረት የመከራውን ዘመን ተሻግረዋል፡፡

ፍቅር ለኢትዮጵያዊያን የጋራ መኖሪያ ጎጇቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በፍቅርና በአንድነት የሚያልፉት የውስጥና የውጭ ጠላት ገጥሟቸዋል፡፡ ጠላት ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ሲመስለው ጦር ይሰብቃል፤ በኢትዮጵያ ላይ ድል ይናፍቃል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲኾኑ ድል እንደማያገኝ፣ ኢትዮጵያንም እንደማይነካ ያውቀዋልና ይከፋል፡፡ የኢትዮጵያዊያን ፍቅር መቀነስ ለጠላት ሰርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እምነት አላቸው፣ ተስፋም አላቸው፣ ፍቅርም አላቸው፣ አሁን ፍቅራቸው የቀነሰ ይመስላልና ከሁሉም የምትልቀውን ፍቅር ማጠንከር ይገባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የአንድ አካል ብልቶች ናቸው፡፡ አንደኛው ለአንደኛው ያስፈልገዋል፡፡ አንደኛው ያለ ሌላኛው መኖር አይችልም፡፡ በአንድነት የተሰጣቸውን ሀገር በአንድነት መቀበል፣ በአንድነት ማስቀጠል፣ በአንድነት ማስረከብና ታሪክ ማውረስ ግድ ይላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያዊያን ጠላቶች ክፉ ነገርን እያደረጉ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ግን ክፉውን በፍቅር ይመልሱ ዘንድ ጥረት ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ማስረዘም የሚሹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪኳ ለፍቅር የተዘረጋን እጅ ታደንቃለች፤ በጥል የተዘረጋን እጅ ግን ትቃዎማለች፡፡

ልጇ ዓባይ እናቱን ያገለግል ዘንድ ሥራ ሲሠራ፣ በብቸኝነት ሲገለገሉበት የነበሩት ሁሉ ተቆጡ፣ ሲደፍሩ ያስፈራራሉ፣ ሲፈሩ ስሞታ ይልካሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በልጄ የማዘዝ መብት አለኝ፤ ከቀደመው መንገዱ ግን ፈጽሞ ቅር አላልኩም እናትህንም ጎረቤትህንም በእኩል አገልግል አልኩ እንጂ ብላለች፡፡ ይህ ቃሏ በማስፈራሪያ አይሻርም፤ በስሞታ አይተውም፡፡ ጥጋብ የወጠራቸው ሰዎችና በጠላቶች ገጸ በረከት የሚቸራቸው ተከታዮች ደግሞ በውስጥና በውጭ ኢትዮጵያን ሲወጥሩ ይታያሉ፡፡ የኢትጵያ ጠላቶች ግንባር እንደፈጠሩ ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም አንድ ኾነው የሚመክቱበት፣ ክብራቸውንና ሉዓላዊነታቸውን የሚያስቀጥሉበት ዘመን መጥቷል፡፡

በዚህ ዘመን አንድ ኾኖ ማበር በብልሃት መሻገር ግድ ይላል፡፡ ማንነትን እስከ ክብሩ ሀገርን እስከ ድንበሩ ኢትዮጵያዊያን ያቆዩት ከሁሉም በፊት ሀገርን በማስቀደማቸው ነው፡፡ በየዘመኑ የተነሱ ኃያላን ነን ባዮች ክንዳቸው ሲፈረጥም ኢትዮጵያን አስገብረው ለመኖር ሞክረዋል፡፡ አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፡፡ አሁን የኅብረት ዘመን ነው፤ የከበደውን ማቅለያ፣ የችግሩን ወንዝ መሻገሪያ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ ʺኢትጵያን በቀኝ ግዛት ለመያዝ የተደጋጋመ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን ለሌላ ባዕድ ሳያስይዙ ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ በአውሮፓም ኾነ በኤሲያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሰፉበት ጊዜ ኢትጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ግን ለማንም ሳይበገሩና ሳይገብሩ እስካሁን ሀገራቸውን አስከብረው ቆይተዋል፡፡” ብሏል፡፡ አባቶችህ እስከዛሬ ካላስደፈሯት አንተስ እስከነገ እንዳትደፈር ምን እያደረክ ነው?

አንድ መኾን ታሪክ ያሠራል፣ አንድ መኾን ከማዕበል ያሻግራል፣ አንድ መኾን የጠላትን አንገት ይሰብራል፤ አንድ መኾን ኢትዮጵያን ያኮራል፡፡ ኢትዮጵያን ከወደድካት በመንገዷ ተጓዝላት፣ ጠላቶቿ የቀደዱትን ቦይ ድፈንላት፣ ድል አድርግና ሠንደቋን ከፍ አድርግላት፡፡ ካከበርካት ታከብርሃለች፡፡ የጀግኖች የደም፣ የቃል፣ የእምነት እዳ አለብህና ዘወትር ኢትዮጵያን አስብ፡፡ ፍጥረታት የሚመኟትን ሀገርህን ጠብቃት፣ ከመደፈር አድናት፤ ክብሯን ከፍ አድርግላት፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

“አብሮነት ሲደራ በተከዜ ዳር ሑመራ”

admin

“የራዲዮ ተደራሽነት ውስን መሆን ለተዛባ የመረጃ ስርጭት መበራከት ድርሻ አለው” ጀማል ሙሃመድ (ዶክተር)

admin

“ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ኃይሎች የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግሥትም ሆነ ከዳያስፖራው ብዙ መሥራት ይጠበቃል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

admin