51.91 F
Washington DC
May 11, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺማንነትን ዳቦ ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ከቀጠለ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን እየቀረበች ትሄዳለች” የታሪክ ምሁሩ አውግቸው አማረʺማንነትን ዳቦ ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ከቀጠለ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን እየቀረበች ትሄዳለች” የታሪክ ምሁሩ አውግቸው አማረ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ዘመናትን በተሻገረው የሥርዓተ መንግሥት ምሥረታ ታሪኳ አያሌ
መልካም ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ የከበዱ የመከራ ዘመናትንም በጥበብ ተሻግራ የሥርዓተ መንግሥት ታሪኳን አስቀጥላለች፤
የግዛት አንድነቷንም አጠናክራለች፤ በየዘመናቱ ገጽታቸውን ለሚለዋውጡ ችግሮችም መፍትሔዎችን እያስቀመጠች በሺህ
የሚቆጠሩ ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ ዘመን ዘመንን እየተካ ሄዶ ኢትዮጵያ ጥበብ የተሞላበት መፍትሔ የሚሹ ችግሮች
ገጥመዋታል፡፡ ለመሆኑ በታሪክ የገጠሟትን ችግሮቿን እንዴት ፈታቻቸው? በተለይም ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ
ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን የፈተኗትን ዋና ዋና ችግሮች በማንሳት የተወሰዱትን የመፍትሔ እርምጃዎችን እንቃኛለን፡፡
አሁን ለገጠማት ችግርስ ከታሪኳ አንጻር ምን አይነት መፍትሔ መውሰድ ይኖርባት ይሆን?
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ድግሪ ተማሪ አውግቸው አማረ በኢትዮጵያ ታሪክ
ውስጥ የታዩ ችግሮች ውስጣዊና ውጫዊ ናቸው፤ በውስጣዊ የሚነሱት ችግሮች መነሻቸው ፖለቲካዊ ኾኖ ማኅበራዊና
ኢኮኖሚያዊ ቀውስን አስከትለዋል፤ መሰረታቸው ኢኮኖሚያዊ ኾኖም ፖለቲካዊ ቀውሶችን አምጥተዋል፡፡ ችግሮቹ መልካቸውን
እየቀያየሩ ይምጡ እንጂ ኢትዮጵያን የሚበትን ችግር አልተፈጠረም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በሺህ ዓመታት የሚቆጠር የሥርዓተ መንግሥት ታሪክ ያላት ሀገር ናት ማለት ተበታትና አታውቅም፣ ቀጣይነት ያለው
የመንግሥት ተቋም ዓላት ማለት ነውም ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሮች በሰላምና በዲፕሎማሲ የተፈቱ ናቸው፣ አልሆን ሲል
ደግሞ በወታደራዊ ኃይልም ችግሮችን እየፈቱ የቀጠሉ ናቸው፡፡ ጊዜ የፈታቸው ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘመናት የገጠሟትን ችግሮች እንደ ዘመናቱ ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረው የግዛት ማስፋፋት ሽኩቻ
ለኢትዮጵያ ችግር ነበር፤ የግጭቶች ሁሉ መነሻ መሬት ኾኖ ግዛቱን በማስፋት የወታደራዊ ኀይሉን ለመጨመርና ለማጠናከር ሲባል
ግጭቶች ተከስተዋል፤ ይህን ለመፍታት የኢትዮጵያ ነገሥታት በግብር መክፈል ላይ መሠረት ያደረገ መፍትሔ ወስደዋል፡፡
ለማዕከላዊ መንግሥት ግብር እንዲከፍሉ እና በሰላም እንዲኖሩ በማድረግ መተማመንን ፈጥረዋል፤ ይህም አንደኛው ወደ
አንደኛው ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ያስቻለ ነበር፤ በዚህ ሁሉ አልሆን ብሎ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ኾኖ ሲገኝ ኃይል
በመጠቀም ችግሮችን መፍታት መቻሉንም ነው ያስታወሱት፡፡
የሕዝብ የግዛት መስፋፋትና ደኅንነት አደጋ ላይ መውደቅ ሌላኛው የኢትዮጵያ ችግር ነበር፡፡ በዚያ የሕዝብ የግዛት መስፋፋት ጊዜ
ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ነበረች፤ ይህንንም ለመፍታት የዘመኑ ነገሥታት ተንቀሳቃሹን ሕዝብ ማስፈር፣ ወጣቱን ወደ መንግሥታዊ
ሥራና ወደ ውትድርና በማምጣት ችግሩን መፍታት ተችሏል ነው የሚሉት፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሳትፎ
እንዳለው ሲሰማው በፍቅርና በጋራ የመኖር አመለካከቱ ስለጨመረ ችግሩን በዚህ መንገድ መፍታት ችለዋል፡፡ በዚሕ ዘመን
ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ነበረች ነገር ግን አልፈረሰችም ነው ያሉት፡፡
በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የካቶሊክ ሃይማኖት መስፋፋትና ያንን ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስን ያነሳሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ንጹሃን አልቀዋል፤ ይህም ከውጭ የመጡ የሚሲዮናዊያንን እንስቀስቃሴ በማስቆም፣ በሃይማኖት መካከል
የተፈጠረውን መከፋፈል በውይይት መፍታት የችግሩ መፍትሔ ነበር ነው የሚሉት፡፡ ነገሥታቱ ሀገሪቱ የግዛት እንድነቷን ጠብቃ
እንድትሄድ የማድረግ ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ችግር በኋላ የግዛት መዳከምና የዘመነ መሳፍንት ዘመን መከሰትን አንስተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የማዕከላዊ መንግሥቱ
መዳከምን ፈጠረ፤ ነገር ግን አካባቢውን ሲመሩ የነበሩት መሳፍንቶች ሀገራቸውን በመጠበቅ በኩል ይሠሩ ነበር፡፡ የግዛት
መዳከሙን ለመመለስ መፍትሔው የዳግማዊ ቴዎድሮስ መምጣትና የማዕከላዊ መንግሥቱ መጠንከር ነበር፡፡ ዳግማዊ አፄ
ቴዎድሮስ ማዕከላዊ መንግሥቱን በማጠናከር በየአካባቢው ጡንቻቸው የፈረጠሙ መሳፍንትን ፈቃደኛ የኾኑትን በሰላም፤
ያስቸገሩትን ደግሞ በወታደራዊ ዘመቻ አስተካክለው የግዛት አንድነቱን ማጠናከር እንደተቻለ ነው የተናገሩት፡፡
የታሪክ መምህሩ አውግቸው አማረ የመሀዲስቶች የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ችግር ኾኖ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይህንንም
ኢትዮጵያዊያን መክተው ያለመሸነፍ ታሪካቸውን አስቀጠሉ ነው ያሉት፡፡
ይህ እንዳለፈም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው አፍሪካን የመቀራመት ዘመቻ በኢትዮጵያም ላይ ተከሰተ፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር
መጣች፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ማሸነፍ እንደሚቻል በማሳየት የዓድዋን ድል አበሰሩ፡፡ ይህም የኾነው
በኢትዮጵያዊያን አንድነትና ጀግነነት ነው፡፡ ዓድዋ ከፋፋይ አጀንዳዎችን ወደ ጎን እንዲተውና ውስጣዊ እኩይ አጀንዳዎች ችላ
እንዲባሉ ያስቻለ መኾኑንም ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው በርካታ ችግሮችን እያለፉ ነው የመጡት፤ይህም አንድነትና አብሮነት ያመጣው ነው፡፡ በዚሁ ዘመን
ሀገሪቱ በረሃብ አለንጋ የተገረፈችበት ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት የታሪክ ምሁሩ ያን ክፉ ቀን በጥበብ መሻገራቸውን ነው ያነሱት፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ኾኖ የሚነሳው የስልጣን ሽኩቻ ነው የሚሉት ምሁሩ የስልጣን ሽኩቻ መስዋዕትነትን
አስከፍሏልም ነው ያሉት፡፡ ሀገርን ወደ ማይኾን ደረጃ ላይ የሚያደርስ ችግር ሁልጊዜ በዲፕሎማሲ ብቻ ላይፈታ እንደሚችልም
ነው ያነሱት፡፡
በድጋሜ የመጣው የጣልያን ወረራም ለኢትዮጵያ የችግር ዘመን እንደነበር ያነሱት ምሁሩ በዚህ ዘመን ጦርነቱን በአንድ ጀንበር
መመለስ ስላልተቻለ በአርበኝነት ሥራ ነጻነት መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡ አርበኞች ጣልያን የቀኝ ግዛት መዋቅር እንዳትዘረጋ
አድርገው ማባረር እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዘውዳዊ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ሠራዊት ወረራም ሌላ ችግር እንደነበር ነው
ያስታወሱት፡፡ በዚህ ፈታኝ ጊዜም ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ የመጣውን ወራሪ ድባቅ በመምታት የግዛት አንድነታቸውን
ማጠናከር መቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግሮች ቢያልፉም አሁን ላይ ያለው ችግር ገዘፍ ይላልም ባይ ናቸው፡፡ ይህም የኢትዮጵያውያን ማሰሪያ
ማኅበራዊ እሴቶች እንዲበጣጠሱ በመደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበራዊ መተሳሰሪያ እሴቶች እንዲያንሰራሩ የተሠራ ሥራ
አለመኖሩም ለችግሩ ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ለማውጣት ችግሩን መለዬት እንደሚገባ የተናሩት የታሪክ
ምሁሩ ሀገሪቱን እዚህ ያደረሳት የስሁት ትርክት ጉዳይ ነው፣ እያንዳንዱ ግጭት ላይ ትርክት አለ፤ ይህን ትርክት ማዬትና
ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ የኢኮኖሚ ስርዓቱንም ማስተካከል ችግሯን እንደሚቀርፈውም አመላክተዋል፡፡ ማንነትን መሠረት ያደረገና ማንነትን ዳቦ
ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ከቀጠለ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን እየቀረበች ትሄዳለች ነው ያሉት፡፡ አሁን ያለው የማንነት ፖለቲካ
አንደኛውን እየጠቀመ ሌላኛውን የሚያስገድል መሆኑ አደጋ ነውም ብለዋል፡፡ አንደኛው ሲበላ ሌላኛው ላይበላ ይችላል፤ ያልበላ
ልጅ መሞት ግን የለበትምም ብለዋል፡፡
ሕግን ሳያስከብሩ ከሌሎች ጋር ለመከራከር አደጋች እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡ ከውስጥ እሳት ጥደን የውጭ እሳት እንመልሳለን
ማለት አይቻልምም ብለዋል፡፡ የማንነት ፖለቲካ ለማንም አይጠቅምም፤ ከዚህ መውጣት ይገባል፤ አንደኛውን የሚበላው እሳት
ቀስ እያለ ሁሉንም ይበለዋል፤ ከዚያ በፊት ሕግን ማስከበር፤ ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ አንድነትን የሚያስጠብቁ ተቋማትን መገንባት
ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በጠንካራ መንግሥትና በሕዝቦቿ መስተጋብር የምትገነባ ናትም ብለዋል፡፡ ለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡም
የሚደነግጥ መንግሥት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ኀላፊነቱን ከተወጣ ኢትዮጵያን ወደ ሰላም የመመለሱ መንገድ
ሩቅ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
አንድ ሰው ሀገር እንደሚያቀናው ሁሉ አንድ ሰው ሀገር እንደሚያፈርስም ነው የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያውያን ተነጣጥሎ የመኖር
ታሪካዊ ዳራ ስለሌላቸው ተያይዘው ከማለቃቸው በፊት በችግሮቻቸው መፍትሔ ዙሪያ ላይ መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
መሥራት የሚገባው ነገር ካልተሠራ ሀገሪቱን ማጣት ላይ ሊደረስ ይችላል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
Previous articleኢትዮጵያና ሩስያ በሰላማዊ የኑክሌር ኃይል አጠቃቀም ያላቸው ትብብር እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡

Source link

Related posts

“እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የሕዝቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት መቻል አለበት እንጂ መወነጃጀል መፍትሔ አያመጣም” መኮንን አለኸኝ (ዶክተር)

admin

ዐብይ አህመድና ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም – መስፍን አረጋ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin

ኢንስቲትዩቱ በተያዘው ዓመት ማብቂያ የሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ይጀምራል

admin