71.89 F
Washington DC
June 22, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺሆሳዕና በአርያም መድኃኒት በሰማይ” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንʺሆሳዕና በአርያም መድኃኒት በሰማይ”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሰው ልጅ ከፈጠረው ይልቅ ያሳተውን ተከተለ፣ ካየው ይልቅ የሰማውን አመነ፤
ከተደረገለት ይልቅ ለሚደረገልት ቋመጠ፣ ከተሰጠው ክብር ይልቅ ገና ሊኖረው ስለሚችለው ክብር ጓጓ፤ በቀብፀ ተስፋ
ከተሰመረለት እውነተኛ መንገድ ወጣ፡፡ በጥቂት ጊዜ ከማይወጣበት የጨለማ ገደል ውስጥም ገባ፡፡ ተሳሳተና የሻተውን ሳያገኝ
የተሰጠውንም አጣ፡፡ ከመልካሙ ፍሬ ተከለከለ፣ ከመልካም ማዕዛም ራቀ፤ ብርሃን ጠፋበት፣ ጨለማ ዋጠው፤ የክብር ልብሱን
አወለቀ፣ የውርድት ልብሱን አጠለቀ፡፡ የተስፋ እንጀራ ሲያበላው የነበረው፣ ከክብርም ክብር እንደሚሆንለት ሲነግረው የነበረው
የክብር ልብሱን አውልቆ ሲዋረድ ሸሸው፡፡
አሳሰቾች አብረው የሚኖሩት እስኪያሳስቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይክዳሉ፡፡ እውነት ናት በሞትም በሕይወትም መካከል
የምትዘልቀው፡፡ የውሸት መንገዷ አጭር ነው፡፡ ቶሎ ታደርሳለች ቶሎም ጥላ ትጠፋለች፡፡ የእውነት መንገድ ግን አድካሚ ናት፡፡
መዳረሻዋ ግን ያማረና የሰመረ ይሆናል፡፡ ከዓለም በፊት ቀደማዊ፣ በዓለም መካከል ማዕከላዊ፣ ከዓለም በኋላም ዳህራዊ የሆነ፤
ዘመን አይቆጠርለትም፣ ጊዜ አይሰላለትም፣ ቦታ አይወሰንለትም፣ ከምንም በፊት ነበር፣ አለ፣ ከምንም በኋላም ይኖራል፡፡
የሚታዬውም የማይታዬውም ዓለም በእርሱ ትወሰናለች እንጂ እርሱ በዓለም አይወሰንም፡፡ ሁሉንም አዋቂ ፤ ሁሉንም ቻይና የትም
ተገኝ ነው፡፡
በዓለም የተነጠፉት ውቅያኖሶች፣ የሚወርዱት የክረምት ዶፎች፣ በእፍኙ አይሞሉም፣ በዓለም ላይ የሚያቃጥሉ እሳተ ገሞራዎች፣
ነዲዶች ሁሉ ተሰባስበው የሰናፍጭ ፍሬ ታክል የምትገለጠውን የመለኮቱን እሳትነት አያክሉም፡፡ እግዚአብሔር አይመረመርም፡፡
መክበርን የወደደው አዳም ያልገመተው ገጠመው፡፡ ኃያል መሆን ሲሻ የተናቀ ሆነ፡፡ መጎናጸፍ ሲሻ የክብር ልብሱን ተነጠቀ፡፡
የከበበው ፀጋ ራቀው፤ መሳቱም ታወቀው፤ የማያቋርጥ የስቃይ እንባ ተናነቀው፡፡ በዳዩ አለቀሰ፡፡ ተበዳዩም ተመለከተው፡፡
ተበድሎም ይክስ ዘንድ ቃል ገባ፡፡ የገባውን ቃል ይፈፅም ዘንድም ወደ ምድር መጣ፡፡ የመዳን ቀን ደረሰ፡፡ ቃል ሰው ሆነ፡፡ ዘር
ሳይቀድመው ያለ አባት በድንቅ ጥበብ ኢየሱስ ተወደለ፡፡ ‹‹ከአባቱ ሳይወጣ መጣ፣ ከአኗኗሩ ሳይለይ ወረደ፣ ከሶስትነቱ ሳይለይ
መጣ፣ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ፣ ከዙፋኑም ሳይለይ በስጋ ልጅ አደረ፣ ከመልዓቱ ሳይወሰን በማሕፀን ተፀነሰ፣ በላይ ሳይጎድል
በማሕፀን ተወሰነ፣ በታችም ሳይጨመርበት ተወለደ›› እንዳለ፡፡
ጥቂት በጥቂት አደገ፡፡የነቢያት ትንቢታቸው አንድ በአንድ ይፈፀም ጀመር፡፡ በምድር አያሌ ታምራትን አደረገ፡፡ ዓለምን ለወጣት፡፡
ወደታች ትቆጥር የነበረችው ዓለም ወደላይ ትቆጥር ጀመረች፡፡ ዓመተ ፍዳ ትል የነበረ ዓመተ ምህረት የምህረት ዘመን አለች፡፡
ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ሄደ፡፡ ያቺም ቀን ሆሳዕና ነበረች፡፡ በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህርና የሊቃውንት
ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላክ ሆሳዕና ማለት በግዕዙ መድኃኒት ማለት ነው፤ በኢብራይስጡ ሆሳኽና ማለት አሁን
አድን ማለት ነው ብለውኛል፡፡ ሆሳዕና በአርያም ሲባል መድኃኒት በሰማይ ማለት ነው፡፡ አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንደኛው ነው፡፡
አብረሃም ይስሃቅን በወለደ ጊዜ የዘንባባ ባዕል አክብሮ ነበር፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ በዘንባባ የተቀበሉበት መንገድ
አብርሃም ይስሃቅን በወለደ ጊዜ እንዳደረገው ነው፡፡ በሆሳዕና ʺአባታችን አብርሃም የተመኛት፣ ያመሰገናት፣ ያከበራት እነሆ
በዓላችን ብሎ የጠራት” እያሉ ያመሰግናሉ ሊቃውንቱ፡፡
ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፥ እንዲህም
አላቸው። ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት ቤተ ፋጌ፡፡ በፊታችሁ ወዳለችው
መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ፣ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች
ቢላችሁ፣ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።
ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሏት
ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፣ አህያይቱንና
ውርንጫዋንም አመጡለት፣ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፣ ተቀመጠባቸውም።
ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ
ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ
ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። ሕዝቡም ይህ ከገሊላ ናዝሬት
የመጣ ኢየሱስ ነው አሉ።
ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ
ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠው፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፣ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት
አላቸው።
ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት
የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን
ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ።
ሊቁ ሲያሜሰጥሩት አህያ የተናቀች ፍጥረት ናት፡፡ አዳምም በበደሉ ተንቆ ነበር፡፡ ዓዳም ወደ መንጠፈ ደይን ወይም ወደ መከራ
ስፍራ ተጥሎ ነበርና የተናቀውን ለማዳን የመጣ ነው፡፡ አህያና ውርንጫ ይዘው መጥተዋል፤ ይህም እናቲቱ የቤተ እስራዔል
ምሳሌ ውርንጫይቱ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናት ነው የሚሉት አበው፡፡ ጌታ በሁለቱም ነው የተቀመጠው፡፡ እናቲቱ በቤተ
እስራኤል የተመሰለችበት ምክንያት እናቲቱ መጫንን የለመደች ናት፤ ቤተ እስራኤላውያንም በሕግ ስር የኖሩ ናቸው ሕገ
እግዚአብሔርን ያውቃሉና ውርንጫዋ መጫን አለመደችም፤ አሕዛብም ከሕግ ውጭ ስለኖሩ ነው ይላሉ፡፡
አህያ ለመስዋዕትነት አትቀርብም፤ የተናቀች ነበረች፤ የሰው ልጅም የተናቀ ነበር፤ ለመስዋዕት ያልበቃችን ፍጡር ተቀምጦባት ወደ
ቤተመቅደስ ገባ፡፡ ይህም አዳምን ወደ ገነት ይዞት እንደሚገባ ሲያመላክት ነው ይላሉ አበው፡፡ ፈታችሁ አምጡልኝ፤ ለጌታም
ያስፈልጉታል በሉ እንዳለ የሰውን ልጅ እንደሚፈልገው ሲያመላክት ነበር፡፡ ፍቷቸው ሲልም ዓለምን በደቀመዛሙርቱ እንዲፈቱ
ስለፈቀደ ነው፡፡
በሆሳዕና ለምን ዘንባባ ተያዘ? በእስራኤል የተከበረ ሰው ሲመጣ ዘንባባ ይያዛል፤ ለጌታም ዘንባባ መያዙ አንደኛውም ምሳሌ ነው፡፡
ለድል አድራጊዎች ዘንባባ ይያዝላቸዋል፡፡ ጌታም ድል አድራጊ ነውና ዘንባባ ተያዘለት፡፡ ዘንባባ እሳት ሲለቁበት ላይ ላዩን ይበለዋል
እንጂ ውስጡ አይነካም፡፡ በክርስቶስ ያመኑ ምዕምናንንም መከራ ቢጠናባቸውም ስጋቸውን እንጂ ነብሳቸውን የሚያቃጥል መከራ
አያገኛቸውም ሲሉ ነው ይላሉ ሊቁ፡፡
ሊቁ “ፍቅርኽ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ጀርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደኽ፡፡ ብዙ ዐይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሰራዊተ
መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሰራዊት ሠረገላ ተቀምጠኽ ክብርኽን ማሳየት አልወደድክም፤
በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኽ ወደ ሰማይ ሰራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል
ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤
በምድርም ደቀ መዛሙርትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን
ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ ርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡” እንዳለ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት መላከል አንደኛው ሆሳዕና ነው፡፡
ቤተክርስቲያንም “በታወቀች በበዓላችን ዕለት በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በመቅደሴ ተራራም ስበኩ ይኽቺ ዕለት የእግዚአብሔር
በዓል ናት፤ በአርያም መድኀኒት የተባልኽ የእስራኤል ንጉሥ አንተ ቡሩክ ነኽ” ትላለች፡፡
የሕጻናትን አንደበት ከፍቶ ተመስግኗልና በታላቅ ደስታ ይከበራል፡፡ በሆሳዕና ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ ቤተመቅደስ ይዞ ገባ፡፡
ይህም ወደ መንግሥተ ሰማያት ይዟቸው እንደሚገባ ምሳሌ ነበር፡፡ በዚያ ቀን ኢየሩሳሌም ሰላምሽ ዛሬ ነው ትባል ነበር፡፡
ሊቃውንቱ ዛሬም ይህንኑ ይላሉ፡፡
ሁሉም ያለው ምንም እንደሌለው በትሕትና ዝቅ አለ፡፡ ትሕትናውን ከእርሱ ተማሩ፡፡ ትሑት ከፍ ይላል፡፡ ትቢተኛ ግን ይዋረዳል፡፡
ሆሳዕና በአርያም መድኃኒት በሰማይ፣ በምድርም ይሁን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
Previous articleእንጅባራ ከተማ ሊገባ የነበረ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፋግታ ለኮማ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ::

Source link

Related posts

ማይክሮሶፍት ለዊንዶውስ ተጠቃሚዎች ወርሃዊ የደህንነት ማዘመኛ ለቀቀ

admin

ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

admin

የአነጋጋሪዋ ቃለ መጠይቅ አድራጊ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው

admin